Friday, February 28, 2014
Co-Pilot Hailemedhen Needs Protection !!
Sunday, February 23, 2014
የረዳት አብራሪ ኃይለመድህን ተግባር
![]() |
| ናትናኤል ካብትይመር |
ናትናኤል ካብትይመር (ኦስሎ ኖርዌይ)
ስለ ረዳት አብራሪ ኃይለመድህን ብዙ ተብሏል ብዙ ተፅፏል ቢሆንም የጀግንነት ተግባሩ ስላኮራኝ እኔም የበኩሌን ልበል። ጥቂቶች በተለይም የወያኔ ህወሃት አባላትና አቀንቃኞች እንዴት ጀግና ይባላል ሲሉ እያስተዋልኩ ነው ፡ ነገር ግን እኔም ሆንኩ በርካታ ሰዎች ረዳት አብራሪውን ጀግና ያልንበት ዋነኛ ምክንያት “በጭቆና ስርዓት ውስጥ ላሉና ብሶታቸውን ማሰማት ላልቻሉ ድምፅ የሆነና ብሶታቸው እንዲሰማ ብሎ ራሱን መስዋዕት ያረገ ሁሉ ጀግና ስለሆነ ነው” እንላለን።
በአየር መንገድም ሆነ በተለያዩ ከፍተኛ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋማት በሚያገለግሉ
ከወያኔ ዘር ወይም አባል ባልሆኑ የተለያዩ ባለሞያዎች ላይ ገሃድ የወጣ የመብት ረገጣ እየደረሰባቸው እንደሆነ እናውቃለን። በማናለብኝነትና
በዕብሪት ላይ የተመሰረተ የመንግስት ጣልቃ ገብነት በርካታ ለሃገር እድገት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ ባለሞያዎችን በአግባቡ አላሰራና
አላፈናፍን ማለቱን ማንም ኢትዮጲያዊ ያውቃል።
የኢትዮጲያ አየር መንገድም በተለያዩ ግዜያት የመንግስት ጣልቃ ገብነት እያማረረው እንደኖረ የቀድሞ የድርጅቱ ዋና ስራ
አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄ በተለያዩ ግዜያት ለመጠቆም ሲሞክሩ አስተውያለው። የኢትዮጲያ አየር መንገድ እንደ አለማቀፍ ድርጅትነቱ
ከሌሎች ሃገራት አምሳያ ድርጅቶች አንፃር ሲታይ የበለጠ የሰራትኞች ስራ መልቀቅ (Employee turnover) በእጅጉ የሚያጠቃው እንደሆነ በርካታ ኢትዮጲያዊያን ያውቃሉ። በርካታ ወጣትና
አንጋፋ ባለሞያዎች በአየር መንገድ በተለያዩ ሞያዎች በአብራሪነት ፣ በበረራ አስተናጋጅነት ፣ በቴክኒሺያንነት ፣ በአስተዳደር ፣
በማርኬቲንግ እና በደንበኞች አገልግሎት ስራ የተሰማሩ ድርጅቱ ለስልጠናና መሰል ክህሎት ማጎልበቻ ከፍተኛ ወጪ ያወጣባቸው ሰራተኞች
ባለው የህወሃት ሰዎች አጉል ጣልቃ ገብነት በፈጠረው መጠነ ሰፊ አስተዳደራዊ በደል ተማረው ስራቸውንና የሚወድዋትን ሃገራቸውን ጥለው
ወደተለያዩ የሌላ ሃገራት አየር መንገዶች ሄደው እንደሚሰሩ የሰነበተ
የአደባባይ ሚስጥር ነው። በወያኔ አስተዳደራዊ መድሎና ብልሹነት በርካታ ለሃገር ጠቃሚ የህክምና ባለሞያዎች ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን
እንዲሁም በርካታ የተለያዩ ክህሎቶች ባለቤት የሆኑ ባለሞያዎችን ሃገራችን ስታጣ መቆየቷ ሁላችንም ስናየው የኖርነው ሃቅ ነው። የእድገት
፣ የስልጠናና የደሞዝ ጭማሪን የመሳሰሉ የሰራተኞች የኑሮ ደረጃና ክህሎት ማሳደጊያ ለተወሰነ ዘርና ሰዎች ብቻ የማረግ ሌሎችን የበይ
ተመልካች በማድረግ መግፋት መረን ወጥቶ በኢትዮጲያ አየር መንገድ ከፍተሻ ሰራተኛ እስከ ዋና ስራ አስፈፃሚ ድረስ የወያኔ ህወሃት
አባላትና አቀንቃኞች መቆጣጠራቸውን በሌሎች መንግስታዊ ተቋማትም እንዲሁ መሆኑን ማንም ኢትዮጲያዊ ያውቃል።
ረዳት አብራሪ ኃይለመድን በአጠቃላይ የወያኔ ህወሃት አካሄድ አጉል የሆነና ሃገርን የሚጎዳ መሆኑ እንዲሁም በተለያዩ
መንግስታዊ ተቋማት የተንሰራፋው አስተዳደራዊ መድሎ በሃገር አቀፍ ደረጃ ስር ሰዶ ሃገራችንን ባለሞያ አልባ እያረጋት እንደሆነ የተረዳ
መሆኑና ለዚህም የጀግንነት ተግባር እንደፈፀመ እንዲሁም ለሌሎች በሃገራቸው ተምረው በሞያቸው ሃገራቸውን ለማሳደግ ፣ ህዝባቸውንም
ለመጥቀምና ለማገልገል አላሰራ ላላቸው ጨቋኝ አገዛዝ ድምፅ መሆኑን ሁላችንም ገብቶን ጀግና ብለነዋል።
አሁንም ሁልግዜም
አምባገነናዊነትን አጥብቀን እንቃወማለን !!
Wednesday, February 19, 2014
የኢትዮጲያ የድህነት አዙሪት መንስኤና መፍትሄዎች “በጥቂቱ” (ክፍል ሁለት)
![]() |
| ናትናኤል ካብቲመር |
ናትናኤል ካብቲመር (ኦስሎ ኖርዌይ)
በክፍል አንድ ፅሁፌ ሃገርንም ሆነ ዜጎችን ከድህነት አዙሪት ለማውጣት አስፈላጊ ስለሆኑት ስለ ማህበራዊ አንድነት እንዲሁም
ስለ ሰብዓዊ መብትና እኩልነት አንዳንድ ነገር ብያለሁ የቀሩትን ዋና ዋና ነጥቦች ደግሞ እነሆ።
የዜጎች ነፃነት
የዜጎች ነፃነት ዘርፈ ብዙ መገለጫ አለው። የዜጎች
ነፃነት ለሃገር ሁለንተናዊ እድገት ሌላው ወሳኝ ግብአት ነው። በጥቅሉ የዜጎች ነፃነት ጥሩ የሆነ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው በፖለቲካዊም
ሆነ በማህበራዊ ዘርፍ አንፃራዊ የሆነ ነፃነት ሲሰፍን ነው። በነዚህ ሁለት ዘርፎች ነፃነት አለው የመባል ደረጃ የደረሰ ማህበረሰብ
ከሌሎች በእጅጉ የተሻለ ምርታማነትን የማሳደግም ሆነ ከድህነት የመላቀቅ እድል አለው። ለመተንተን እንዲመች ፖለቲካዊና ማህበራዊ
ነፃነትን ለየብቻ ላስቀምጣቸው።
ሀ. ፖለቲካዊ ነፃነት
ዜጎች በሃገራቸው ፖለቲካ ውስጥ በግልም ሆነ በቡድን የሚንቀሳቀሱበት ፣ ለሃገራቸው ይጠቅማል ብለው ያመኑበትን ሃሳብ በተለያዩ መድረኮች ወይም ሚዲያዎች የሚገልፁበትን አሰራር እንደመንግስት የተቀመጠው ቡድን ወይም አካል የመቅረፅ ሃላፊነት አለበት። የዚህ አይነት አሰራር አለመኖርና የዜጎች የፖለቲካ ነፃነት ታፍኖ እንደወንጀል መቆጠር ለሃገር እድገትና ምርታማነት የመረባረብና የመጨነቅ ባህልን ከዜጎች አመለካከት ያጠፋና ከፍተኛ የሆነ የፍርሃት ስሜት በጠቅላላ ማህበረሰብ ላይ እንዲሰፍን ያደርጋል።
ከዚህ መሰል የአፈና ስርዓት ከሚፈጥረው ፍርሃት በመጠኑም ቢሆን የተላቀቁ የማህበረሰብ አባላት ለሃገር ምርታማነትና እድገት ቢውል ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖርውን አቅማቸውን ፣ እውቀታቸውን አንዲሁም ግዜና ገንዘባቸውን ባስ ሲልም ህይወታቸውን ለዜጎች የፖለቲካ ነፃነት መከበር ይሰዋሉ። በተቃውሞ ሰልፎችና የፖለቲካ ክርክሮች የበርካታ ዜጎች ውድ ግዜ ይባክናል። እንደ ኢትዮጲያ መንግስት ያሉ አምባገነኖችም የመብት ጥያቄዎችንና አማራጭ ሃሳቦችን የሚያመነጩ አካላት ማስራቸውን ፣ ማዋከባቸውን ባስ ሲልም እንደህዝብ ጠላት መቁጠራቸውን ይቀጥላሉ። እዚህ ደረጃ ላይ ነው እንግዲህ የፖለቲካ ነፃነት መጥፎ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው።
የዜጎች የፖለቲካ ነፃነት አለመከበር የአንድን ሃገር የፖለቲካ ምህዳር ያጠባል እንዲሁም ከፖለቲካ በተያያዘ የፍርሃት መንፈስ ያነግሳል። ይህ ደግሞ ሰፋ ካለ የፖለቲካ ምህዳር ከሚሳተፉ አቅም ያላቸው ዜጎች የሚመነጩ ሁነኛ የሃገር እድገት አምጪና ምርታማነትን አሳዳጊ እይታዎች ከናካቴው እንዲጠፉ ያደርጋል። ሃገርም በተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድን አመለካከትና ፍላጎት ብቻ መመራት ትጀምራለች። ከዚህ መሰል ሃገራዊ አመራር ዜጎችን ከድህነት አዙሪት መላቀቅ መጠበቅ በአንድ እጅ እያጨበጨቡ ድምፅ መጠበቅ ማለት ነው።
ለ. ማህበረሰባዊ ነፃነት
በአንድ ሃገር ወይም አካባቢ ተሰብስበው የሚኖሩ ማህበረሰቦች በሃገር ወይም መንግስት ደረጃ ከተደነገገው ህግ ባሻገር ሲወርድ ሲዋረድ የኖረ ያልተፃፈ ህግ አላቸው። ማህበረሰባዊ ነፃነት በጥቅሉ የዛ ማህበረሰብ አባላት ውስጥ አንዱ ያንዱን አመለካከት፣ ግላዊ ማንነት እንዲሁም እምነት የሚያከብርበት የተፃፈም ሆነ ያልተፃፈ የነፃነት መርህ ነው። ይህ የማህበረሰብ ነፃነት ለፖለቲካ ነፃነት እንደ አይነተኛ ግብዓትም ያገለግላል። ዜጎች የተለያዩ ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ አጀንዳዎችን እያነሱ በተዘጋጁም ሆነ ባልተዘጋጁ የማህበራዊ የውይይት መድረኮች ተቃራኒ ሃሳቦችን በመከባበር ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽሩበትና የሚከራከሩበት ፍላጎታቸውን በነፃነት ሌላውን ባለመጫን ወይም መብቱን ባለመጋፋት የሚገላለፁበትን ባህል ካጎለበቱ ፡ ይህም ባህል ሃገራዊ መልክ ከያዘና ወደ መንግስት ደረጃ ካደገ በውይይትና በበሳል ክርክር የተፈተነ ሃሳብ ነጥሮ ይወጣና ሃገርን የማሳደግ ህልም እውን ይሆናል።
ይህ ተቃራኒ ሃሳብን የማዳመጥና የማንሸራሸር ባህል ከማህበረሰብ ወደ መንግስት ደረጃ የማደግ ወይም ከመንግስት ወደ ማህበረሰብ የመስረፅ እድል አለው። ከማህበረሰብ ወደመንግስት የሚያድገው የዛ ማህበረሰብ አባላት ሁለንተናዊ ማህበረሰባዊ እድገት ለማምጣት በሚል ተነሳስተው በነፃነት የራሳቸውን መንግስታዊ አካል ሲያዋቅሩ ወይም በቀላል ቋንቋ መንግስታቸውን ሲመርጡ ነው። በዚህ መልኩ ለስልጣን የበቃ መንግስት የመረጠውን ህዝብ ለማገልገል ስለተነሳ የህዝቡን ነፃነት አያፍንም ባህሉን እንደጠበቀ ይቀጥላል። ነገር ግን እንደ ሃገራችን ኢትዮጲያ አይነት በህዝብ የተመረጠ መንግስት ማለት ምን አይነት እንደሆነ በታሪካቸው አጋጥሟቸው የማያቁ ሃገራት መንግስት ላይ የማህበረሰባዊ ነፃነት ባህልን ማሳደር እጅግ ከባድ ይሆንባቸዋል።
በጦርነት ወይም በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት አብዛኛውን ግዜ በማንነትም ሆነ በሃሳብ ልዩነት ላይ የተመሰረቱ ነፃ የሆኑ ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ውይይቶች ባህልን አሳድጎ ወደ ህዝብ ሲያሰርፅ አይታይም። የሃገራችን መንግስት የሚያደርጋቸው የሃሳብ ነፃነትን የማፈን ሂደትና እንዲሁም አማራጭ ሃሳብ አመንጪና የመብት መከበር ጠያቂ አካላት ላይ የሚያደርገው ኢሰብአዊ ተፅዕኖ በተጠቂዎች ላይ ከሚፈጥረው የአካልና የስሜት ጉዳት ባሻገር እጅግ አሳሳቢ የሆነው በተለያየ የማንነት ወይም የርዕዮተ አለም ልዩነት የሚፈጠሩ ማህበራት አባላትና ደጋፊዎች
መካከል አንዱ አንዱን እንደጠላት የማየት እንድምታን ባስ ሲል ደግሞ የርስ በርስ ግጭትን መፍጠሩም ነው። ይህ ደግሞ በዜጎች መከባበርና መዋደድ ላይ የተመሰረተ መተባበር ብቻ ሊገኝ የሚችለውን የምርታማነት መጨመርና እድገትን እንዲሁም ከድህነት አዙሪት የመውጣት ጥረትን በከፍተኛ መልኩ ያቀጭጨዋል።
ዘላቂነት ያለው የፖለቲካ ስርዓት
ሁነኛ የፖለቲካ ስርዓት ማለት በጥቅሉ አንድን ሃገር ወይም ማህበረሰብ የአገዛዝና አስተዳደራዊ መዋቅር በአለማቀፍ ደረጃ ከተቀመጡት ስርዓቶች ጋር በማዛመድ ለዛ ሃገርና ማህበረሰብ እንዲመች ተደርጎ የተቀረፀ ማለት ነው። በፖለቲካ ስርዓት ዜጎች መንግስት እንዲሆን በመረጡት ወይም መንግስት ሆኖ በተቀመጠው አካል ጤናማና ሚዛናዊ
የሆነ የህግና ስርዓት ፣ የኢኮኖሚ ስርዓት ፣ የባህላዊና ማህበረሰባዊ ስርዓት የማዋቀርና የማስተዳደር ሃላፊነት ሲሰጡት ያም መንግስት ዘላቂነት ያላቸው ህግጋትና ፖሊሲዎችን ለመረጠው የፖለቲካ መንገድና ለማህበረሰቡ እሴቶች በሚስማማ መልኩ ቀርፆ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የአገዛዝ ስርዓት ሲመሰርትና ይህንንም ለማስከበር በአግባቡ ሃላፊነቱን ሲወጣ ማለት ነው።
በአለማችን በርካታ ሃገራት ለዜጎቻቸውና ለነባራዊ ሁኔታቸው በሚመች መልኩ የፖለቲካና የአገዛዝ ስርዓት ገንብተዋል ለአብነት ለመጥቀስ ያህልም የአሜሪካ መንግስት የሚከተለው የፖለቲካ ስርዓት ከሁለት ምዕተ አመት በላይ መሰረታዊ መርሁን ሳይለቅ ሊቀጥል ችሏል። ከዚህም ወጥነት ካለው የፖለቲካ ስርዓቱ የመነጩት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ስርዓቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እየጠነከሩ አሁን ላሉበት ደረጃ ደርሰዋል። በአንፃሩ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ያላደጉ ሃገራት ለአለማደጋቸው እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኛው የሆነው በየግዜው የሚቀያየር ስርዓት መኖሩ እንዲሁም ጭራሽ ይህ ነው የሚባል ስርዓት አለመኖሩ ነው። በኢትዮጲያ የሚመጣው መንግስት ሁሉ የራሱን ስርዓት እንደ አዲስ መጀመሩ ከፖለቲካው ስርዓት
ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን የኢኮኖሚና ማህበረሰባዊ ስርዓቶች እንደገና ፈርሰው እየተሰሩ የተወሰኑትም “የቀደመው መንግስት አሻራ አለባቸው” በሚል ምክንያት እየፈረሱ አጠቃላይ የሃገር እድገትን ባለበት እንዲሄድ አርጎታል።
የአሁኑ የኢትዮጲያ መንግስት ስልጣኑን በእርስ በርስ ጦርነት አግኝቶ ያዋቀረው የአገዛዝ ስርዓት ስልጣኑን ያገኘው በህዝብ ምርጫ ስላልሆነ ስርዓቱ ለተወሰኑ የማህበረሰቡ አካላት ብቻ ሲያደላ ቆይቷል። በዚህም ሳቢያ መጠነ ሰፊ የሆን የፍትህ መጓደል ይስተዋላል። ከማህበረሰብ ውይይትና ይሁንታ ውጪ ስልጣኑን ለማደላደል የሚያወጣቸው የተለያዩ ህግጋት በህዝብ ዘንድ በግድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሲያደርግ የለየለት አምባገነን ሆኗል።
እንደ ኢትዮጲያ መንግስት አይነት አምባገነናዊ ባህሪይ ያላቸው መንግስታት በተለየ መልኩ አማራጭ የፖለቲካ ስርዓት ወይም በተመሳሳይ ስርዓት የተለዩ ዝርዝር ፖሊሲዎችን ይዘው ለተነሱ የፖለቲካ ማህበራት በግልፅ ውይይትና ክርክር ማንኛቸው ለህዝብ እንደሚሻሉ ከማሳየት ይልቅ አማራጭ ሃሳብ አመንጪዎችን ይዘው የተነሱትን አላማ ለህዝብ እንዳያስተዋውቁ በማፈን ፣ በማዋከብ ፣ በማሰርና ውድ ህይወትን እስከመንጠቅ ይደርሳሉ።
የኢትዮጲያ መንግስት የራሱን ፖሊስዎችና መርሆች በግልም ሆነ በህዝብ ሚዲያ እንደልቡ እያስነገረ ነገር ግን አማራጭ የፖለቲካ ማህበራትን መሰብሰብ እስከመከልከልና ብሎም እንደ ህዝብና ሃገር ጠላይ ይፈርጃል። ይህ መረን የወጣ አምባገነናዊ ስርዓት ዜጎች ሃገራዊ እድገት ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎ አሳንሶ በገዛ ሃገራቸው ባይተዋር የሚያደርግ እንዲሁም ሃገርን ከድህነት የማውጣት ጥረት እጅግ ጠቃሚ ተሳትፎ እንዳያረጉ የሚያስቀር ለተወሰኑ ቡድንና ግለሰቦች የስልጣን ጥምና ጥቅም ሲባል ሃገርን የድህነት አዙሪት ውስጥ የመዝፈቅ ሃላፊነት የጎደለው ስርዓት ነው።
አስተማማኝ የኢኮኖሚ መዋቅር
የኢኮኖሚ መዋቅር ወይም ስርዓት ማለት በጥቅሉ በአንድ ሃገር ወይም ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ምርትና አገልግሎትን የማምረትና የማሰራጨት እንዲሁም የተለያዩ ግብዓቶችን በተገቢው መልኩ የማዳረስ ስርዓት ማለት ነው። በዚህ ስርዓት ውስጥ የማህበረሰቡን
የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች አቅራቢ ተቋማት ፣ ማህበራትና ድርጅቶች እንዲሁም ተጠቃሚዎች መካክል ጤናማ የሆን ፍሰት እንዲኖር
የሚያደርግ ስርዓት ማለት ነው። ይህም ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር የተስተካከለና ጤናማ እንዲሆን መንግስት የተለያዩ ህግጋቶችንና ድንጋጌዎችን
በማውጣት ከአለማቀፍ ኢኮኖሚ ስርዓቶች ጋር የማጣጣም ሃላፊነት አለበት።
ጤናማ የኢኮኖሚ ስርዓት መኖር የአንድን ማህበረሰብ
ወይም ሃገር የኑሮ ደረጃ በማሳደግ በኩል ቀጥተኛ አስተዋፆ አለው። ኢኮኖሚያዊ መዋቅሩ በተገቢው መልኩ እንዲቀጥል ሰላማዊና በፍላጎት
ላይ የተመሰረተ ሃገራዊ አንድነት መኖር ወሳኝ ሚና አለው። አንድ መንግስትም የሃገርን ኢኮኖሚ በተገቢ መልኩ እየመራ ነው የሚባለው
አጠቃላይ ፍሰቱን ለሁሉም ዜጋ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሲያስተዳድር ፣ ሲዳኝ እንዲሁም ሲያበረታታ ነው።
ፍሰቱ ሚዛናዊ አደለም የሚባለው ለተወሰኑ የንግድ
ተቋማት መንግስታዊ የሆነ አድልዎ በማድረግ የተቀሩትን የመጫን ሂደት
ሲኖር እንዲሁም ኢኮኖሚውን የማስተዳደር ሃላፊነት የተሰጣቸው መንግስታዊ ተቋማት በገለልተኝነት በማስተዳደር ፈንታ በአድሎአዊነት
ጣልቃ ሲገቡና በጥቅማ ጥቅም ሲያዙ ነው። ይህ ሚዛናዊነቱን የማሳት ተግባር ለተወሰኑ ግለሰቦች ጥቅም ሲባል በሃገር ኢኮኖሚ እድገት
ላይ ከፍተኛና ቀጥተኛ ሚና የሚኖራቸውን ድርጅቶችን ለክስረትና ለመዘጋት ይዳርጋል ፣ ሃገርና ህዝብ ከንግድ ፍሰቱ የሚያገኙትን ጥቅማ
ጥቅሞች ያሳጣል ፣ ወደ ንግድ ስራዎችና መሰል እንቅስቃሴ ለመግባት ያቀዱ ሃገራዊም ሆነ አለማቀፋዊ ድርጅቶችን ፍላጎት ይገታል ፣
የስራ አጡን ቁጥር ይጨምራል እንዲሁም በርካታ መሰል ችግሮችን በመፍጠር ሃገር ወይም ማህበረሰብ ከድህነት አዙሪት ለመውጣት የሚያረገውን
ጥረት ያቀጭጨዋል።
ለምሳሌ በሃገራችን ኤፈርት የተባለው የንግድ ተቋም
በመንግስት በሚደረግለት ግልፅና ቀጥተኛ ድጋፍ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስ ፣ ከዛ ሁሉ የኢትዮጲያ ብሄርና ክልል አንድ ክልልና
ብሄርን ለማልማት በሚል የተዋቀረ ድርጅት አለ። የዚህ ድርጅት በተለያዩ ውድድር በሚያሻቸው የንግድ ዘርፎች ተሰማርቶ ነገር ግን
በመንግስት ድጋፍ በሞኖፖል መንቀሳቀሱ ሌሎች ቀድመው የነበሩ እንዲሁም አዲስ የሚፈጠሩ የንግድ ተቋማትን ምን ያህል እንደጎዳ በዘርፉ
ባለሞያዎች ብዙ ተብሏል። መሆን የነበረበት ግን የኢትዮጲያ መንግስት እከተለዋለው ያለውን የኢኮኖሚ ስርዓት በአግባቡ ቢያስተዳድር
፣ ጤናማ የውድድር መንፈስ ቢፈጥር እንዲሁም የሁሉንም ሃገራዊ ድርጅቶች ምርቶች ከአድልዎ ውጪ በሆነ መልኩ አለማቀፍ ገበያ ውስጥ
እንዲታወቁ በቅንነት ቢጥር ሃገራችን በቅርቡ ከድህነት አዙሪት ትወጣ ነበር።
እንግዲህ ከተነሳሁበት ሃሳብ ስፋትና ጥልቀት አንፃር በእኔ አቅም ይህችን ብያለው። አንባቢዎች የማይስማሙባቸው ወይም የቀረ የሚሉት ብዙ ሊኖር ይችላል ነገር ግን እኔ ሃገር የምትገነባው በጎ መሰረት ያለው ግልፅ ውይይት ሲኖር ነው ብዬ ስለማምን እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ ይህችን አዋጥቻለሁ።
ሃገራችን ከአምባገነናዊ ስርዓት የምትላቀቅበትን ህዝቦቿም ከድህነት አረንቋ የሚወጡበትን ቀን ቅርብ ያርግልን !!
Subscribe to:
Comments (Atom)

