Friday, May 1, 2015

አይሲስ በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ የፈፀመው ግድያ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ

በአዲስ አበባ ኀዘኑን ለመግለጽ የወጣው ህዝብ ድብደባ ደረሰበት
ISIS massacre on Ethiopian Christians in Libya
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. April 21, 2015)፡- ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ የሚኖሩ 30 ኢትዮጵያውያንን በጥይት በመደብደብ እና በካራ በማረድ አይሲስ (ISIS) የተባለው አሸባሪ ቡድን በፈፀመው ግድያ በሀገር ቤትና በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከፍተኛ ኀዘን ላይ ወድቀዋል። ይህንን ግድያ አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘግይቶ የኀዘን መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በመግለጫውም በመላው ሀገሪቱ ለሦስት ቀናት ብሔራዊ ኀዘን ሆኖ እንዲቆይ እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤምባሲዎች ጭምር የሚገኙ ባንዲራዎች ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ አዟል።
ይህ ከፍተኛ ኀዘን ያደረሰው አሰቃቂ ግድያ የተፈጸመው በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው የቃጠሎ ግድያ፣ የንብረት ማውደም ጥቃት ውሎ ሳያድር በመሆኑ ለሀገራችን ህዝብ ተደራራቢ ኀዘን ሆኖበታል።
ISIS massacre on Ethiopian Christians in Libya
በሊቢያ አሸባሪ ቡድኑ በሚንቀሳቀስበት አቅራቢያ የቤታቸውን በር ዘግተው የሚገኙት ሌሎች ከ90 በላይ ኢትዮጵያውያን መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን ሊታወቅ ባለመቻሉ ሌላው አሳሳቢ ችግር መሆኑ ታውቋል። እነዚሁ ከአይሲስ ተደብቀው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የድረሱልኝ ጥሪ እያቀረቡም ይገኛሉ። እነዚሁ ሴቶችና ወንዶች ሆነው በተለያየ ክፍል ተደብቀው የሚገኙ ወገኖች ላለፉት ሦስት ቀናት ምግብ ማግኘት እንዳልቻሉ ለመረዳት ተችሏል።
Addis Ababa: Protest on ISIS massacre on Ethiopian christians in Libya
ዛሬ ረፋዱ ላይ ብሶትና ኀዘን የፈነቀለው የአዲስ አበባ ነዋሪ ድንገተኛ ሰልፍ አድርጎ ወደ መስቀል አደባባይ ተሟል። ሰልፈኛው የሟች ልጆቹንና ወገኖቹን ፎቶ በመያዝ ጩኸቱን እያሰማ የወጣ ሲሆን፣ በዚህ ባልታሰበ ሰልፍ ያልተደሰቱት የመንግሥት ባለሥልጣናት የፖሊስ ኃይል በማሰማራት አደባባይ የወጣውን ህዝብ በዱላ እየደበደቡ በመኪና ሲጭኑት ተስተውለዋል። እስካሁን ድረስ ሰልፈኛውን ለመበተን በተደረገው እርምጃ የቆሰለውንና ታፍሶ የተወሰደውን ቁጥር ለማወቅ አልተቻለም።
Addis Ababa: Protest on ISIS massacre on Ethiopian christians in Libya
ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የውጪ አገር ከተሞች ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው ቤተክርስቲያናት በመሰብሰብ ወገኖቻቸውን በጸሎት አስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የዋሽንግተን ነዋሪዎችን ጨምሮ በግሪክና በሌሎችም አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ ዐረቢያና በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ጽ/ቤቶች በመሰለፍ የተደረገውን ግድያ በማውገዝ፤ በጭፍጨፋው የተሰማሩት ለፍርድ እንዲቀርቡ እና እርምጃም እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግድያውን በማውገዝ መግለጫ አውጥታለች። ቤተክርስቲያኗ በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ የሚደርስን ጥቃት እንደማትፈቅድና እንደምትቃወም ገልጻ፤ ይህ የአሸባሪዎች እርምጃም ማንኛውንም ኃይማኖት የማይወክል በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት ማውገዝ ይገባቸዋል ብላለች። ከዚህም ሌላ ይኸው በሀገር ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶሱ ከነገ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ቀናት ፀሎተ ምህላ እንዲደረግ አዝዟል።
”ድምጻችን ይሰማ!” በሚል የሚታወቁትና በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፣ ”በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ በደረሰው ጭካኔ የተመላበት ግድያ አዝነናል” የሚል መግለጫ በማውጣት ድርጊቱን ማውገዛቸው ታውቋል። በተለያዩ አገራት በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም በተለያዩ የማኅበራዊ ድረገጾች በወገኖቻቸው ላይ በደረሰው አሰቃቂ ግድያ የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ከመግለጻቸውም ባሻገር፤ አይሲስ እስልምናን አይወክልም ሲሉ ተደምጠዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ይንንኑ ግድያ በማውገዝ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅቶች የተቃውሞ መግለጫ አውጥተዋል። በአውሮፓና በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች ከሐሙስ ጀምሮ የተቃውሞ ሰልፎች ለማድረግ ጥሪ ተላልፏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ ኢትዮጵያ በዜጎቿ ላይ ለደረሰው ጥቃት የአፀፋ እርምጃ በአሸባሪው ቡድን ላይ የምትወስድ ከሆነ ግብጽ ለእርምጃው ተባባሪ እንደምትሆን በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስ አሳውቀዋል። ከደቡብ አፍሪካና ከሊቢያ ግድያ ውጭ በየመን ከፍተኛ አደጋ እያንዣበበባቸው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እንዳሉ አይዘነጋም። ይህ ሣምንት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ጭለማው ሣምንት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

መንግስት እራሱ በጠራው ሰልፍ ያሰራቸውን ፍርድ ቤት አቀረበ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
• ‹‹የታሰርነው የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆናችን ብቻ ነው›› የሰማያዊ ፓርቲ አባላት
• ‹‹የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን ሊያሳስር አይገባም›› ዳኛው
መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስ ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን የጭካኔ እርምጃ ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ላይ ፖሊስ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል›› በሚል የያዛቸውን የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ሌሎችም በርካታ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ሚያዝያ 16/2007 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች አቀረበ፡፡ ከእነዚህ መካከል ቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በርካት ያሉት ታሳሪዎች ቀርበዋል፡፡ በነ ወይንሸት ሞላ የምርመራ መዝገብ 12 ታሳሪዎች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ዳንኤል ተስፋዬና ኤርሚያስ ጸጋዬ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡ በተጨማሪም በእነ ወይንሸት የምርመራ መዝገብ ከቀረቡት 12 ታሳሪዎች መካከል 7ቱ ሴቶች ሲሆን በሌሎች ተናጠል መዝገቦችም ሴቶች ቀርበዋል፡፡ በቄራ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ከቀረቡት መካከል 5ቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
በታሳሪዎቹ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ ማነሳሳት›› የሚል ክስ ያቀረበው ፖሊስ ምርመራዬን አልጨርስኩም በሚል 14 ቀን ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ የነበር ቢሆንም ዳኛው በበኩላቸው ‹‹14 ቀን ብዙ ነው፡፡ ለምርመራ 6 ቀን ይበቃል፡፡ በመሆኑም በ6 ቀን ውስጥ የምትመረምሩትን መርምራችሁ የምትለቁትን መልቀቅ አለባችሁ›› በሚል 6 ቀን ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡ ወይንሸት ሞላ ‹‹የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለሆንኩ ብቻ ነው የተያዝኩት፡፡ ሰልፍ ሳይጀመር ነው የተያዝኩት፡፡›› ስትል ፖሊስ ያቀረበውን ክስ ስትቃወም በተመሳሳይ ዳንኤል ተስፋዬ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ አባል ስለሆንኩ ብቻ ሰልፉ ካበቃ በኋላ ነው ታድኜ የተያዝኩት›› ሲል ክሱን ተቃውሟል፡፡ ዳኛው በበኩላቸው ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆናችሁ የታሰራችሁ ካላችሁ የሚጣራ ይሆናል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን ሊያሳስር አይገባም፡፡ ይህን ፖሊስ መመርመር አለበት›› ብለዋል፡፡
ከእነ ወይንሸት በተለየ መዝገብ ነገር ግን በተመሳሳይ ክስ የቀረበበትና የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ማስተዋል ፈቃዱ 10 ቀን ተቀጥሮበታል፡፡ በመሆኑም እነ ወይንሸት ሚያዚያ 22 ቀን እንዲሁም ማስተዋል ፈቃዱ ሚያዚያ 26 ቀን ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል ኢንጅነር አምሃ ታደሰ የተባለ ግለሰብ ቪዲዮ ሲያነሳ እንደተያዘ ቢገልጽም ፖሊስ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት›› የሚል ክስ አቅርቦበታል፡፡ በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ከሰዓትም የሚቀርቡ ታሳሪዎች እንዳሉ ታውቋል፡፡
በሌላ የፍርድ ቤት ዜና ሰልፉ ካለቀ በኋላ ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ በፖሊስ ታድኖ የተያዘው ብሩክ የኔነህ የተባለው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ዛሬ አራዳ የፌደራል ምድብ ችሎት ቀርቦ 12 ቀን የተቀጠረበት ሲሆን ሚያዝያ 28/2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቤት ተበረበረ፡፡አራት ኪሎ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላችሁ›› በሚል መታፈሳቸውን ገለጹ


ሰልፍ ሳይጀመርና ከሰልፉ በኋላ ተይዘው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቤት ተበረበረ፡፡

አራት ኪሎ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች ትናንት ሚያዝያ 22/2007 ዓ.ም ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላችሁ›› በሚል ለሁለተኛ ጊዜ መታፈሳቸውን ወጣቶቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ 

ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ሳይጀመርና ከሰልፉ በኋላ ተይዘው የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ቤት ተበረበረ፡፡ ካሳንቺስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ትናንት ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ቀርበው የ6 ቀን ቀጠሮ ከተሰጠባቸው በኋላ ምሽት ላይ ቤታቸው መበርበሩንና ንብረቶቻቸው መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

በብርበራው ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በሰላማዊ ሰልፍና በሌሎች አጋጣሚዎች የሚለብሱት የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ የምርጫና ሌሎች ቅስቀሳ ወረቀቶችም ለ‹ምርመራ› ተወስደዋል፡፡
ቤታቸው ለሰዓታት የተበረበረባቸው ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ማስተዋል ፍቃዱ ሲሆኑ ወይንሸት ሞላ የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ወረቀቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ ሲዲዎች፣ አርማ የሌለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ (በተናጠል አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የሆነ)፣መጽሐፎች እና ሌሎችም ህጋዊ ሰነዶች እንደተወሰዱባት ገልጻለች፡፡ ዳንኤል ተስፋዬ የሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አርማ ያለበት ቲሸርት፣ በአንድ ላይ ያስጠረዛቸው የፋክትና የአዲስ ጉዳይ እትሞች፣ ሲዲዎችና ካሴቶች ተወስደውበታል፡፡ በተመሳሳይ ኤርሚያስ ጸጋዬ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተር፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሰነዶች፣ ሲዲዎች፣ ማስታወሻ ደብተሮችና ሌሎችም ህጋዊ ሰነዶች ተወስደውብኛል ብሏል፡፡

አራት ኪሎ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች ትናንት ሚያዝያ 22/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ መታፈሳቸውን ወጣቶቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ከአንድ ወር በፊት ፖሊስ ወጣቶቹን ቪዲዮና ኳስ የሚታይባቸው ቤቶች ውስጥ እያሉ ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላችሁ›› በሚል ካሰረ በኋላ አስፈርሞና አሻራ ወስዶ እንደለቀቃቸው ገልጸዋል፡፡
በትናንትናው ዕለትም ፖሊስ በርከት ያሉ ወጣቶችን አስሮ የነበር ሲሆን ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ እንድትበጠብጡለት ምን ያህል ብር ይከፍላችኋል? ማን ነው ያደራጃችሁ? ደንጋይ ለመወርወር ምን ያህል ብር ይከፈላችኋል?›› በሚል ምርመራ እንደተደረገባቸው ገልጸዋል፡፡ በስተመጨረሻም ምሽት ላይ አስፈርሞና አሻራ ወስዶ ከእስር ተለቀዋል፡፡ ወጣቶቹን ‹‹ከአሁን በኋላ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ግንኙነት እንዳላችሁ ካወቅን በሽብር ነው የምንከሳችሁ፡፡›› የሚል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡